መጀመሪያው የሳይክል መልዕከት የማድረስ አገልግሎት ለበርካታ ወጣቶች ተስፋን ሰንቋል!


የሥራ አጥነት ቁጥር እንደሚያሳስበን ያክል በጥረታቸው ከራሳቸውም አልፎ ለሌሎችም የእንጀራ ገመድ የዘረጉ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታትና ለሌሎችም መነቃቃት ምክንያት እንዲሆኑ ለማስቻል የሚሰራው ሥራ አነስተኛ መሆኑ የዚያኑ ያህል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ እናምናለን።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሥራ ፈጠራን የሚያበረታቱ ጭላንጭሎች ቢስተዋሉም አሁንም ቢሆን የራስን ሥራ ፈጥሮ መስራት መሰናክሉ ብዙ ነው። በተለይ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶች ዓመታትን በለፉበት ትምህርት ሥራ ፈጥረው ለመንቀሳቀስ አስቻይ የሆኑ በሮች አሁንም ክፍት አይደሉም።
ይህን የሚፈቅዱ አስቻይ ህጎች ቢኖሩና ሁኔታዎች ቢመቻቹ ለብዙ ወጣቶች ጥቅሙ እልፍ ቢሆንም ይህንን በጽናት ተሻግረው ለሌሎችም የተረፉ ወጣቶች ቁጥር ቀላል የሚባልም አይደለም። የእነዚህን ወጣቶች ተሞክሮ ማጋራት ለሌሎችም መንገዱን መጠቆም ነውና ቲክቫህ ኢትዮጵያም ለዛሬ ለ1000 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዓላማ ካነገቡ አቬኒር ቴክኖሎጂስ “ትኩስ” ጋር ቆይታ አድርገናል።
የድርጅቱ መስራቾች ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በ2010 የተመረቁ 6 አብሮ አደግ ወጣቶች ናቸው። ተስጧቸውም ሆነ ዝንባሌያቸው ወደ ኮምፒውተርና ሶፍትዊር ቴክኖሎጂ በመሆኑ ገና በትምህርት ቤት ሳሉ “የድርጅት ባለቤት መሆን አይቻልም ወይ?” በሚል ቁጭት ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ሃሳቦች ላይ መመካከርን ምርጫቸው አደረጉ፡፡